ማን ነን?
ራዕያችን
ወንጌልን በሀይል እና በስልጣን የምትሰብክ; ለቅዱሳን (አማኞች) መታደስ: መለወጥ እና ዕለት ዕለት ጌታን ወደመምሰል እንዲያድጉ የምትተጋ; በመንፈስ ቅዱስ የምትመራ: የእግዚአብሔር ቃል ባለስልጣን የሆነባት:
ጌታን በናፍቆት የምትጠበቅ; ሞዴል የሆነች የክርስቶስን ቤተክርስቲያን ማየት::
የእምነት አቋም
- ስድሳ ስድስቱ የብሉይና ሐዲስ ኪዳን መጽሐፍት ቅዱሳን ሰዎች በእግዚአብሔር መንፈስ ተነድተዉ እግዚአብሔር ለሰዉ ልጆች ማንነቱንና መለኮታዊ ሐሳቡን የገለጠበትና ያሰፈረበት፣ የማይወድቅና የማይሳሳት፣ የእምነትና አኗኗር መሠረት፣ ብቸኛና ፍጹም፣ እንዲሁም የመጨረሻ ስልጣን ያለዉ መሆኑን እናምናለን (2ጢሞ 3፣16)።
- በእግዚአብሔር አብ፣ በእግዚአብሔር ወልድ እና በእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ አንድ አምላክ እናምናለን (ማቴ 28፣19 እና 2ቆሮ 13፣13)።
- መፍጠር፣ ሥነ-ፍጥረትን መጠበቅ፣ መዋጀትና የመጨረሻዉ ፍርድ የእግዚአብሔር ፍጹም ስልጣንና የበላይነት እንደሆነ እናምናለን (ሮሜ 5፣12-18)።
- በመንፈስ ቅዱስ በተጸነሰ፣ ከድንግል ማርያም በተወለደ፣ ፍጹም አምላክ፣ ፍጹም ሰዉ በሆነው የሰዎች ብቸኛ አዳኝ በሆነው በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ እናምናለን (ሉቃ 1፣26-35፣ ዮሐ 1፣14-18፣ ኢሳ 7፣14፣ 9፤6)።
- 4..5 ክርስቶስ ለሃጢያታችን እንደ ሞተ፣ እንደ ተቀበረ፣ በሦስተኛዉም ቀን እንደ ተነሳና ለደቀመዛሙርቱ እንደታየ እናምናለን ( 1 ቆሮ 15፣1-4፣ ሮሜ 4፣25)።
- ኢየሱስ በአካል ወደ ሰማይ እንዳረገ፣ በእግዚአብሔር ቀኝ በክብር እንደ ተቀመጠ፣ ዳግም በአካል እንደሚመጣ እናምናለን (ዮሃ 14፣2-3፣ 1ተሰ 4፣13-18)።
- የእግዚአብሔር ልጅ የኢየሱስ ክርስቶስ ቤዛዊ ሞትና ትንሣኤ ብቻ ሰውን ከሃጢአት ዕዳና ቅጣት እንደሚያድን እናምናለን። ሰው በእግዚአብሔር ፊት መጽደቅ የሚችለውም በእግዚአብሔር ጸጋ ብቻ እንደሆነ እናምናለን (ኤፌ 2፣8-9፣ ዕብ 9፣12፣ 22፣ ሮሜ 5፣11)።
- በጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ትእዛዝ መሠረት በአብ፣ በወልድና፣ በመንፈስ ቅዱስ ስም በማጥመቅ እናምናለን (ማቴ 18፣28-29፣ ሐዋ 2፣34-36፣ 19፣1-6)።
- በድነት ጊዜ በሚሆን የመንፈስ ቅዱስ ጥምቀት እናምናለን። በድነት ጊዜ ወይም ከድነት በሁዋላ በሚሆን የመንፈስ ቅዱስ ሙላት እናምናለን (ሐዋ 2፣1-4፣ 10፣44-46፣ ገላ 14፣15)።
- በጥንቷ ቤተ ክርስቲያን የነበረው የመንፈስ ቅዱስ ስጦታ ዛሬም ባለችው ቤተ ክርስቲያን እንደሚሰራ እናምናለን (1ቆሮ 12፣14)።
- አማኞች ጌታ ዳግም እስኪመጣ ድረስ የጌታን እራት በህብረት በመካፈል የክርስቶስን ሞት መናገር እንዳለባቸው እናምናለን (ሉቃ 17፣20፣ 1ቆሮ 11፣23-26)።
- 4.12 እግዚአብሔር ሰይጣንን እና ተከታዮቹን በፍርድ ቀን ወደ ዘላለም እሳት እንደሚጥላቸው እናምናለን (ይሁዳ 6))።
- እግዚአብሔር ለአማኖች የዘላለም ህይወትን፣ ለሃጥአን ደግሞ የዘላለም ቅጣትን እንደሚሰጥ እናምናለን (ማር 9፣43-48፣ 2ተሰ 1፣9፣ ራእ 20፣10-15 ዮሐ 5፣24፣ 3፣16)።
- በአንዲቷ ዐለማቀፋዊት ቤተ ክርስቲያን እናምናለን። ይህች ዐለም ዐቀፋዊት ቤተ ክርስቲያን የብዙ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያናት ውጤት እንደሆነችም እናምናለን። እያንዳንዱ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን በገዛ ራሳቸው ሉዐላዊ ሆነው በክርስቶስ አገዛዝ ስር እንደሚደራጁ እናምናለን (ኤፌ 1፣22-23)።
- ስልጣን ሁሉ ከእግዚአብሔር ዘንድ እንደሚሰጥ፣ ባለስልጣኖችም ለእኛ መልካም የእግዚአብሄር አገልጋዮች ሆነዉ እንደተሾሙ እናምናለን (ሮሜ 13፣1-23)።
- ክርስቲያናዊ ጋብቻ ከጊዜ ጋር የማይለዋወጥ የእግዚአብሔርን ቃል እዉነት መሠረት ያደረገ በቃሉ እንደ ተደነገገዉ በአንዲት ሴትና በአንድ ወንድ መካከል ብቻ በቃል ኪዳን የሚፈጸምና እግዚአብሔር ያቋቋመዉ ህብረት እንደሆነ እናምናለን። እግዚአብሔር ግብረ ሥጋ ግንኙነትን የፈቀደዉ በጋብቻ በተሣሰሩ ወንድና ሴት መካከል ብቻ እንደ ሆነ እናምናለን። በመሆኑም ዝሙት፣ ምንዝርና፣ ግብረ ሰዶማዊነት፣ እንስሣን መገናኘት፣ ዘመድን ማስነውር፣ ሴሰኝነት፣ ወይንም ጾታን መለወጥ በጌታ ፊት የተጠላ መሆኑን እናምናለን። በመሆኑም፣ ቤተ ክርስቲያናችን በጌታ ባመኑ አንድ ወንድ እና አንዲት ሴት መካከል ብቻ ጋብቻን ትፈጽማለች (ዘፍ 1:28-29፣ 2:18-25፣ ማቴ19፣1-9፣ ማር 10፣2-9፣ ኤፌ 5፣25 ሮሜ 1፣27)።
ተልዕኮ
- ወንጌልን በክብር እና በሀይል: በግልም: በህብረትም በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ መስበክ::
- በአንድ ወቅት በእግዚአብሔር ቤት ጌታን ሲያመልኩ እና ሲያገለግሉ የነበሩ አሁን ግን በተለያየ ምክንያት ከእግዚአብሔር ቤትና ህብረት የራቁ ቅዱሳንን ወደ ቤቱ መሰብሰብ እና ወደ አገልግሎት ማሰማራት::
- የእግዚአብሔርን ቃል ሙሉ ባለስልጣንነት ወደ ቤተክርስቲያን መመለስ::
- የመንፈስ ቅዱስን አመራርና አሰራር በቤተክርስቲያን በሙላት መግለጥ::
- በአካሉ ውስጥ ያሉ የክርስቶስ ብልቶች እንደስጦታቸው (እንደፀጋቸው) በየቦታቸው እንዲሰሩ ማሰማራት::
- ቅዱሳን በዕለት ተዕለት የግል ህይወታቸው በእውነተኛ የክርስቶስ ደቀመዝሙርነት ህይወት እንዲመላለሱ: ጌታን እየመሰሉ ወደፍፁምነት ሙላት እንዲያድጉ እና ዳግመኛ መምጣቱን (ምፅአቱን) በናፍቆት እየጠበቁ እንዲኖሩ መርዳት::
- ሙሽራውን የምትጠባበቅ ቤተክርስቲያንን ለጌታ ቀን ማዘጋጀት::